የኮምቦልቻ ከተማ የንጹህ መጠጥ ዉሃ ተደራሽነት፣ ብክነትና ብክለት ያተኮረ ዉይይት ተካሄደ

N3የኮምቦልቻ ከተማ የመጠጥ ዉሃና ፍሳሽ አገልግሎት ጽ/ቤት ባዘጋጀዉ በዚህ የዉይይት መድረክ በዉሃ አቅርቦትና ተደራሽነት፣ የዉሃ ብክነትና ብክለት እንዲሁም አዲስ በሚጀመረዉ የማስፋፊያ ፕሮጀክትን ትኩረት ተደርጎ ዉይይት ተደርጓል፡፡ ዉይይቱን በእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያሰጀመሩት የከተማዉ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር አህመድ የሱፍ እንዳሉት የከተማ አስተዳደሩ ለዉሃ አገልግሎት ጽ/ቤቱ በተገቢዉ መንገድ ዉሃ ለህብረተሰቡም ሆነ ለኢንዱስትሪዎች እንዲያደርስ ከፍተኛ እገዛ እያደረገ እንደሆነና ዉሃ አገልግሎቱም ይህንን እገዛ በመጠቀም የተሻለ የዉሃ አቅርቦት እየሰጠ ይገኛል፡፡ አዲስ የሚጀመረዉን የማስፋፊያ ፕሮጀክትም በስኬት በማጠናቀቅ ይበልጥ ተደራሽነቱን የሚያሰፋ ይሆናል ብለዋል፡፡

የአብክመ ዉሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ልማት ቢሮ የመጠጥ ዉሃ አቅርቦት ተ/ዳይሬክተር አቶ አስራት ካሴ በከተማ ዉሃ አገልግሎቱ አጠቃላይ እንቅስቃሴ፣ በአዲሱ የማፋፊያ ፕሮጀክት ግንባታ ያዘጋጁትን ጽሁፍ ሰፋ ያለ ጊዜ ወስደዉአቅርበዋል፡፡ የቀረበዉን ጽሁፍ መሰረት በማድረግም በርካታ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከተሰባሳቢዎች ቀርበዋል፡፡ ከተነሱት ዉስጥም ዋና ዋናዎቹ፡-
• የኮምቦልቻ ከተማ በክልል ደረጃ አርዓያና ሞዴል የሆኑ ስራዎችን እየሰራ የሚገኝና በርካታ ጠንካራ ጎኖች ያሉት ቢሆንም ከተደራሽነት፣ የዉሃ ብክነትና ብክለት ላይ አሁም መስራት እንደሚጠበቅበት በአንክሮ ተጠቅሷል፣

 • የህብረተሰቡን ፍላጎትና ጥያቄዎችን በመፍታት ረገድ በከተማዉ ከሚገኙ የመንግስት ተቋሞች በግምባር ቀደም የሚጠቀስ ነዉ፣
 • ተቋሙ ከከርሰ-ምድር የዉሃ ሃብት ከማሰብ በተጨማሪ የገጸ-ምድር ሃብቱንም ትኩረት ሊያደርግ ይገባል /ቦርከና ወንዝ/
 • የኮምቦልቻ ከተማ ከሌሎች የክልሉ ከተሞች የተለየ ትኩረት ሊደረግለት ይገባል-የኢንዱስተሪ ቀጠናና የደረቅ ወደብ አገልግሎት መስጫ በመሆኑ፣
 • የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃና ማልሚያ ቦታ ሊመቻች ይገባል፣ የፍሳሽ አወጋገድ ስርዓቱም ማዘመን ያስፈልጋል፣
 • ከፍተኛ ዉሃ የሚጠቀሙ ተቋማት /ኢንዱስትሪዎች/ በራሳቸዉ ገንብተዉ ሊጠቀሙ ይገባል፣
 • መንገድ፣ ዉሃ፣ ቴሌ እና መብራት ተቀናጅተዉ መስራት አለባቸዉ፡፡ አንዱ ሲሰራ ሌላዉ እያፈረሰ እንዲቀጥል ማድረግ የለብንም፣
 • የከተማዉ ዉሃ መስመር መረጃ አልተያዘም፡፡ በመሆኑም የማሰራጫ መስመሮች የሚገኙበት ቦታ በተደራጀ መልኩ ሳይት ፕላን ተዘጋጅቶ መቀመጥ መቻል አለበት፣
 • አንድ የዉሃ ጉድጓድ ሲቆፈር የሌላዉን ጉድጓድ የዉሃ የመስጠት አቅም ተፅዕኖ እየደረሰበት በመሆኑ በጥናት ቢመለስ፣
 • ተቋሙ ይበልጥ የሚሰጠዉን አገልግሎት ለማዘመንና የተሻለ ለማድረግ በእዉቀት ላይ ተመስርቶ ስራዎችን ሊሰራ ይገባል፣
 • ከዉሃ ተደራሽነት አንጻር በተለይም የገጠር ቀበሌዎችን /6/ ተደራሽ ለማድረግ ጥረት ማድረግ አለበት
 • በዚህ መድረክ ጽ/ቤቱ ያሉትን በጎ ነገሮችና ችግሮች እንድናዉቅ አድርጓል፤ ሊበረታታ ይገባል፣
 • መብራት ሲጠፋ ዉሃ አብሮ ይጠፋልና አማራጭ ጀኔሬተሮች ሊኖሩ ይገባል፣ የሚሉና ሌሎች ጥያቅዎችና አስተያየቶች ተነስተዋል፡፡

በዉይይቱ የተገኙት የቢሮዉ ምክ/ሃላፊ አቶ ይመር ሃብቴ በበኩላቸዉ ዉሃ አገልግሎቱ የተሻለ ተቋም ለመገንባት ሶስት መመዘኛዎችን ማሳካት ያስፈልጋል - የዉሃ ጥራት፣የዉሃ አቅርቦት /ብዛት/ እንዲሁም ለሁሉም ተደራሽ ማድረግ ይጠበቅብታል፡፡ የዉሃ መገኛ ቦታዎችን በአግባቡ አስከልሎና ከንኪኪ አጽድቶ ጥበቃ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል፡፡
የቢሮዉ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ አቶ አደም ወርቁ በበኩላቸዉ አሁን በስራ ላይ ያለዉ ታሪፍ አነስተኛ በመሆኑና ብድሩና መመለስ በሚያስችል መልኩ መጠናት ስላለበት ትኩረት እንዲደረግበት አሳሰበዉ የደንበኛ ቁጥር መጨመር፣ የዉሃ ተጠቃሚዎች ፎረምን ማጠናከርና ወደ ስራ ማስገባት እንዲሁም ዘመናዉ የአስራር ስርዓት እንዲኖር ማድረግ ትኩረት ተሰጥቷቸዉ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡
የአብክመ ዉሃ፣መስኖና ኢነርጂ ልማት ቢሮ ሃላፊ ዶ/ር ማማሩ አያሌዉ ዉይይቱን ሲዘጉ እንደተናገሩት የኮምቦልቻ ከተማ በራስ ጥረት የከተማዉን ህብረተሰብ ጥያቄና የኢንዱስትሪዎችን የዉሃ ፍላጎት አስተማማኝ በሆነ መልኩ ለማቅረብ የሚያደርገዉ ጥረት ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዉ ለዚህም ስኬት የከተማ አስተዳደሩን ድጋፍ አድንቀዋል፡፡ ከተሞች የወደፊት የዉሃ ፍላጎትን ሲያጠኑ የከተማዉ ህዝብ ቁጥር ብቻ ሳይሆን የኢንዱስትሪ መስፋፋትንም ጭምር ታሳቢ አድርገዉ መሆን እንዳለበት አመላክተዋል፡፡ ዩኒቨርስቲዉም በማህበረሰብ አገልግሎቱ ሙሉ ዉሃዉን እያገኘ ያለዉ ከዉሃ አገልግሎቱ በመሆኑ ከጥናት ጀምሮ የተለያዩ ቁሳቁሶችና /ማቴሪያሎችን/ እንዲሁም የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በመስጠት ሊደግፍ ይገባል፡፡ የዉሃ ጥራት ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠዉ የሚገባ ነዉ፤ እንደክልልም እጥረቶች እንዳሉብን ተረድቻለሁ ማስተካከል ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በመጨረሻም እንደ ቢሮ ለኮምቦልቻ ከተማ የሚያስፈልገዉን ማናቸዉም ቴክኒካል ድጋፎች ሳንሰለች የሚሰጥ መሆኑና በሚሰሯቸዉ የማስፋፊያ ስራዎች ከጎናቸዉ መሆናቸዉን አበክረዉ አስገንዝበዋል፡፡
በዚህ የዉይይት መድረክ ከአብክመ ዉሃ፣መስኖና ኢነርጂ ልማት ቢሮ ሃላፊዎችና ዳይሬክተሮች፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶች፣ የወሎ ዩኒቨርሲቲ፣ የዉሃ ተጠቃሚዎች ፎረም፣ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችና የምክር ቤት አባላት፣ የዉሃ አገልግሎቱ አመራሮች ተካፋይ ሲሆኑ ከአዳራሽ ዉይይት በተጨማሪ የዉሃ ተቋማት ጉብኝት ተካሂዷል፡፡

መጪ ዝግጅቶች

No events

ጎብኚዎችን ቆጣሪ

032539
ዛሬ
ትናንት
በዚህ ሳምንት
ባለፈው ሳምንት
በዚህ ወር
ባለፈው ወር
ጠቅላላ
20
40
60
32366
1146
865
32539