Message of the Bureau Head

image

ዶ/ር ማማሩ አያሌዉ ሞገስ

የአብክመ ዉሃ፣መስኖና ኢነርጂ ልማት ቢሮ ሃላፊ

የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ልማት ቢሮ የክልሉን የውሃ ሃብት ማስተዳደር፣ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ማቅረብ፣ ከአነስተኛ እስከ መካከለኛ ደረጃ ያሉ የመስኖ አውታሮችን በመገንባት ለተጠቃሚው ህብረተሰብ ማስተላለፍና የአማራጭ ኢነርጂ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅና በማቅረብ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ከክልሉ መንግስት የተሰጠው ተግባርና ሃላፊነት በመሆኑ ይህን ተግባርና ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችል ሰፊ ስራ እየሰራ ይገኛል፡፡

በሁለተኛዉ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋን በገጠር ሁሉም አርሶ አደር ከሚኖርበት አካባቢ ከ1 ኪ/ሜ በላይ ሳይጓዝ 25 ሊትር ዉሃ በቀን ለእያንዳንዱ ሰው፤ በከተማ የህዝብ ቁጥራቸዉ ከ20,000 እስከ 999,999 ህዝብ ለሚኖርባቸዉ የክልላችን ከተሞች  ከ50 እስከ  80 ሊትር ዉሃ በቀን ለሰዉ ለማዳረስና  የህዝብ ቁጥራቸዉ ከ20,000 በታች ለሆኑ የክልላችን ከተሞች በ250 ሜትር ርቀት 40 ሊትር ዉሃ በቀን ለሰዉ ለማድረስ የተቀመጠዉን አዲስ  ስታንዳርድ መሰረት በማድረግ የተጣለዉን ግብ ለማሳካት ሰፊ ርብርብ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

 

በዚህም መሰረት ከላይ በተቀመጠዉ ስታንዳርድ በዕትዕ-2 መጀመሪያ የንጹህ መጠጥ ዉሃ ሽፋናችን በገጠር 53.46% በከተማ 54% እንደ ክልል 53.54% ላይ የደረሰ ሲሆን ከዚህ በመነሳት በአምስት ዓመት የተቀመጠዉን ግብ ለማሳካት ከፍተኛ ስራ ተሰርቶ በከተማም ሆነ በገጠር የንጹህ መጠጥ ዉሃ ሽፋኑን ከፍ ማድረግ ተችሏል፡፡ ይህ አመት የሁለተኛዉ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን አቅድ ዘመኑ ማጠናቀቂያ በመሆኑ ከፍተኛ የንጹህ መጠጥ ዉሃ ችግር ያለባቸዉን፣ ዉሃ ያልደረሰባቸዉንና ተጀምረዉ ሳይጠናቀቁ ረዥም ጊዜ የወሰዱ ፕሮጀክቶችን በመለየት ለመገንባትና ለማጠናቀቅ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን እንገኛለን፡፡ በዚህም ሂደት በርካታ የንጹህ መጠጥ ዉሃ ፕሮጀክቶች ተጠናቀዉ ለህብረተሰቡ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ፡፡

ይህ ዘርፍ ከፍተኛ መዋዕለ-ንዋይ የሚጠይቅ፣ በከፍተኛ ደረጃ የተማረ የሰዉ ሃይልና  አዳዲስ ቴክኖሎጅ የሚያስፈልገዉ መሆኑና ከጊዜ ጊዜ እያደገ የመጣዉ የህብረተሰብ ፍላጎትና የከተሞች መስፋፋት ተደማምሮ የዘርፉን ስራ በተግዳሮት የተሞላ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መፍለቂያ አድርጎታል፡፡ ሆኖም ያሉንን ሃብቶች በአግባቡ በመጠቀምና የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ ንጽህናዉ የተጠበቀ እና በቂ ዉሃ ለህብረተሰባችን ለማድረስ ከመቼዉም ጊዜ በተሻለ ተግተን እየሰራን እንገኛለን፡፡

የክልሉን ህብረተሰብ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ተደራሽ ከማድረግ በተጨማሪ በመስኖ ልማቱ ዘርፍ ሀገሪቱ ወደ መካከለኛ ገቢ ካላቸዉ አገራት ተርታ ለመሰለፍ የምታደርገዉን ጉዞና የድህነት ምጣኔዉን ለመቀነስ በሚደረገዉ እልህ አስጨራሽ ትግል ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ የመስኖ አዉታሮችን በመገንባት ላይ እንገኛለን፡፡ በዚህም ዛሬ ላይ በርካታ የመስኖ ተቋማት ተገንብተዉ በዘርፉ የተሰማሩ አርሶ አደሮች በአመት ሁለት ጊዜና ከዚያ በላይ ማምረት በመቻላቸዉ እራሳቸውን ከመመገብ ባለፈ ለሌላው የሃገሪቱ ዜጎች ምርታቸውን ለገበያ አቅርበው በገቢ ረገድም ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል፡፡  አሳታፊ የሆኑ የመስኖ ጥናት፣ ዲዛይንና ግንባታ ስራዎችን በማካሄድ፣ የመስኖ ተቋማት ዘላቂ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ የአስተዳደር ስርዓት በመዘርጋትና የህብረተሰቡን ግንዛቤ ከፍ በማድረግ ከዚህ በፊት በአመት አንድ ጊዜ ብቻ ያመርት የነበረው የአርሶ አደር ማህበረሰባችን በአመት ሁለትና ከዚያ በላይ አምርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል፡፡ በዚህ አመትም ባለፉት አመታት ተጀምረዉ ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግና በተለያዩ ምክንያቶች የቆሙ ፕሮጀክቶችን ወደ ስራ ማስገባት ትኩረት ሰጥተን እየሰራን እንገኛለን፡፡

የመጠጥ ዉሃም ሆነ የመስኖ ተቋማትን መገንባት ብቻ ስኬታማ መሆን አይቻልም፡፡ ዘለቄታዊና አስተማማኝ በሆነ መልኩ ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ በዚህም መሰረት በተለያዩ ምክንያቶች ተበላሽተዉና በአስተዳደራዊ ችግሮች ምክንያት የቆሙ ተቋሞችን ችግር ፈቶ ወደ ስራ ማስገባትና ሁሉም ተቋማት በዘላቂነት አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ላይ ቢሮዉ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል፡፡ በመሆኑም የመስኖና የመጠጥ ዉሃ ተቋማት ተጠቃሚዉ ህብረተሰብ ባለቤት ሁኖ እንዲጠብቃቸዉ፣ እንዲንከባከባቸዉና በኔነት ስሜት እንዲያስተዳድራቸዉ ለማስቻል ባለፉት አመታት የተጠቃሚዎች ማህበራትን በማቋቋም ከፍተኛ ለዉጦችን አስመዝግበናል፡፡ የተቋማት የብልሽትና የዉሃ ብክነት ምጣኔንም ለመቀነስ ጥረት እየተደረገ ነዉ፡፡ በሌላ በኩል ከከተሞች ዕድገት ጋር እያደገ የመጣዉን የከተሞች የዉሃ ፍላጎት በዘላቂነት ለመፍታት ከተሞች ለዉሃ ግንባታ የሚወጣዉን የኢንቨስትመንት ወጪ ታሳቢ ያደረገ ታሪፍ በማዘጋጀት የኢንቨስትመንት ወጪን በማስመለስ በኩል ከነ ክፍተቶቹም ቢሆን መልካም ዉጤቶች ተመዝግበዉበታል፡፡

ከኢነርጅዉ ዘርፍ አኳያ የተፈጥሮ ሀብታችንን ለመጠበቅና በዘላቂነት ለመጠቀም አማራጭ የኢነርጂ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም አስፈላጊ ነዉ፡፡ በመሆኑም በቀላል ቴክኖሎጂ ወደ ህብረተሰቡ ማዳረስ የሚቻልባቸዉን የፀሀይና ነፋስ ኃይል፣ የባዮ ጋዝና የተሻሻሉ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን በማስፋፋትና በስፋት እንዲሰራጩ በማድረግ የህብረተሰቡ የኑሮ ደረጃ እንዲሻሻል እያደረግን እንገኛለን፡፡  እነዚህንና ሌሎች መሰል ተግባራት  በአንድ ተቋም በሚደረግ ጥረት ብቻ መፍታትና ውጤታማ መሆን ስለማይቻል ሁሉም ባለድርሻ አካላት በተለይም የህብረተሰቡ፣ የተቋራጭና አማካሪ ድርጅቶች ፣ ለጋሽና አበዳሪ ድርጅቶች፣ በየደረጃው የሚገኙ የአስተዳደር አካላትን ጨምሮ ከፍተኛ ርብርብ የሚጠይቅ ስለሆነ፤ የክልሉን ህዝብ የንፁህ መጠጥ ዉሃ አቅርቦት ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስና ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ የመስኖ አውታሮችን በመገንባትና የኢነርጅዉን ዘርፍ በማልማት የህብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል  ርብርብ እናደርጋለን፡፡

 

 

Upcoming Events

No events

Visitors Counter

027590
Today
Yesterday
This Week
Last Week
This Month
Last Month
All days
274
82
527
26748
989
1301
27590